አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት መደረግ ይጀምራሉ፡፡
ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ የፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን በሜዳው ቦዶ ግሊምትን ያስተናግዳል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት በመጀመሪያ ዙር ያደረጉትን ጨዋታ የኖርዌዩ ክለብ ቦዶ ግሊምት 3 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን አስፍቷል፡፡
ቦዶ ግሊምት በዚህ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ክስተት ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
የኖርዌዩ ክለብ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሻምፒየንስ ሊጉ ማንቼስተር ሲቲ፣ ኢንተር ሚላን እና አትሌቲኮ ማድሪድን የመሳሰሉ ትልልቅ ቡድኖችን ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡
የቦዶ ግሊምት እና የስፖርቲንግ ሊዝበን የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከአርሰናል እና ባየር ሊቨርኩሰን አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡
በሌላ የዛሬ መርሐ ግብር ምሽት 5 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል፡፡
በሳንቲያጎ ቤርናባው በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሪያል ማድሪድ በፌዴሪኮ ቫልቬርዴ ሦስት ግቦች 3 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ 13ኛ የእርስ በርስ ግንኙነታቸው ነው፡፡
በሎስ ብላንኮዎቹ በኩል በጉዳት የመጀመሪያው ጨዋታ ያመለጣቸው ኪሊያን ምባፔ፣ አልቫሮ ካሬራስ፣ ዴቪድ አላባ እና ጁድ ቤሊንግሀም ዛሬ ምሽት ማንቼስተር ሲቲን የሚገጥመው የሪያል ማድሪድ የቡድን ስብስብ ውስጥ ተካትተዋል።
የማንቼስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከዛሬ ምሽት ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ በትናንትናው ዕለት ለተጫዋቾቻቸው እረፍት መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከባየርን ሙኒክ እና አታላንታ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡
ሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ ቼልሲ በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የፈረንሳዩን ፒኤስጂ በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል፡፡በፓርክ ደ ፕሪንስ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ፒኤስጂ 5 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት ሁለቱ ቡድኖች በሻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ተገናኝተው ፒኤስጂ በድምር ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ቼልሲን ከውድድሩ ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከሊቨርፑል እና ጋላታሳራይ አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡
አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ከባየር ሊቨርኩሰን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሌላኛው የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር ነው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በባይ አሬና ያደረጉትን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አንድ አቻ ያጠናቀቁ ሲሆን፥ በድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆነው ክለብ በሩብ ፍጻሜው ከቦዶ ግሊምት እና ስፖርቲንግ ሊዝበን አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

