አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 18ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ኢራን በኢራቅ ባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ፈፅማለች፡፡
በኤምባሲው ላይ ዛሬ ጠዋት የተፈጸመው የድሮን ጥቃት ከዚህ ቀደም ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጠንከር ያለ መሆኑን የኢራቅ የደህንነት ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ߵዘመቻ ለእውነተኛ ቃል ኪዳንߴ የሚል ስያሜ በሰጠው ጥቃት በኳታር የሚገኘውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ኢላማ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በእስራኤል የተለያዩ ከተሞችና በመካከለኛው ምስራቅ ዘጠኝ ሀገራት በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት ፈፅማለች፡፡
እየተካሄደ ባለው ጦርነት የአሜሪካ ጦር ወደ 5 ሺህ በሚጠጉ የኢራን ባህር ኃይል፣ ወታደራዊና የነዳጅ መሰረተ ልማት ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አስታውቋል፡፡
18ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ከኢራን ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከእስራኤል 15 ሰዎች፣ 13 የአሜሪካ ወታደሮች እንዲሁም የጥቃት ኢላማ በተደረጉ ሌሎች ሀገራት 49 ያህል ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ እስራኤል እና አሜሪካ በሊባኖስ እየፈጸሙት በሚገኘው ተደጋጋሚ ጥቃት 886 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡
ከማህበራዊ ቀውሶች በተጨማሪ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደረ የሚገኘው ጦርነቱ በተለይም በነዳጅ አቅርቦትና ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ይገኛል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ሰርጥን ለማስከፈት የተለያዩ ሀገራት የባህር ሀይል ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ለፕሬዚዳንቱ ጥሪ ምላሽ የሰጠ ሀገር የለም መባሉን ቢቢሲ፣ ፕረስ ቴቪ እና አልጀዚራ ዘግበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

