አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ለማከናወን የአደጋ ስጋትን አስቀድሞ ማመላከት ይገባል አለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም፡፡
ፎረሙ በጋሞ ዞን ተከስቶ በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 6 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል፡፡
አርባ ምንጭ፣ ጂንካ፣ ወላይታ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎችን ያቀፈው ፎረሙ የተለያዩ ምርምሮችን በማከናወን የተፈጥሮ አደጋ የቅድመ መከላከል ስራዎችን ለመደገፍ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር) በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፥ ዩኒቨርሲቲዎቹ ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን ለተፈጥሮ አደጋዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እየሰሩ ይገኛሉ።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ከዚህ ቀደም በመሬት መንሸራተት ዙሪያ በጋራ የጀመሩትን ምርምር በማጠናከር የማህበረሰቡን ሕይወት ለመታደግ ኃላፊነት ወስደዋል ነው ያሉት፡፡
በተራራማ አካባቢዎች በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ አደጋ ሊፈጥሩ በሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ዙሪያ የምርምር ስራዎች እንደሚከናወኑም ተመላክቷል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጉዳዮች ሰፊ ጥናታዊ ምርምር ስራዎችን በማከናወን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደዚህ አይነት የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ቀድሞ ለመከላከል የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በመለሰ ታደለ

