አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሴንትራል ባንኪንግ የሚያዘጋጀውን የማዕከላዊ ባንክ ክፍያና የገበያ መሰረተ ልማት ግንባታ ሽልማት አሸነፈ፡፡
ባንኩ በኢትዮጵያ ቁልፍ የፋይናንስ ገበያ መሠረተ ልማቶች ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይጠበቅበት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም በሀገሪቱ የፋይናንስ መሰረተ ልማት ላይ ወሳኝ ማሻሻያ ማድረጉን ሴንትራል ባንኪንግ አስታውቋል።
ከፈረንጆቹ 2024 ወዲህ ሀገሪቷን ወደ ወለድ ተኮርና የዋጋ ንረት ተኮር የገንዘብ ፖሊሲ በማሸጋገር በገበያ ላይ ወደተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ማሸጋገሩም ነው የተገለጸው።
ለአብነትም የግምጃ ቤት ገበያና የካፒታል ገበያ ውጥኖችን ማስተዋወቅን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አመልክቷል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ሽልማቱ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ አማካኝነት የገበያ መሠረተ ልማትን በማሳደግ እንዲሁም የገንዘብ ፖሊሲ ስርጭትንና ዘላቂ ልማትን በማጠናከር ይበልጥ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡

