አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ሰይድ ሙጅታባ አሊኻሚኑ ሀገራቸው በቁልፍ መሪዎቿ ላይ ለተፈጸሙት ግድያዎች የአጸፋ ርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል፡፡
12 የአረብ እና እስላማዊ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በበኩላቸው ኢራን በቀጣናው ሀገራት ላይ እየፈጸመቻቸው ያሉት ጥቃቶች እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡
የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ም/ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ ባሳለፍነው ማክሰኞ በእስራኤል በተፈጸመባቸው ጥቃት የተገደሉ ሲሆን፥ የቀብር ስርዓታቸው በርካታ ኢራናውያን በተገኙበት በትናንትናው ዕለት በቴህራን ተፈጽመዋል፡፡
ጠቅላይ መሪው አያቶላህ ሰይድ ሙጅታባ አሊኻሚኑ ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ መልዕክት መሰል ግድያዎች ይበልጥ ጠንካራ ያደርጉናል ብለዋል፡፡
ገዳዮቻችን የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ ሀገራቸው በቁልፍ መሪዎቿ ላይ የአጸፋ ርምጃ እንደምትወስድ ማስጠንቀቃቸውን ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአረብ እና እስላማዊ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢራን በቀጣናው ሀገራት ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በቀጣናዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ፥ በኢራን ተፈጽመዋል ያሏቸውን ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ኮንነዋል፡፡
የጋራ መግለጫውን ያወጡት ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን፣ ጆርዳን፣ አዘርባጃን፣ ግብጽ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ፓኪስታን፣ ኳታር፣ ሶሪያ፣ ቱርኪዬ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ናቸው፡፡
ኢራን በነዳጅ መሰረተ ልማቶች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎችና ሌሎች የንጹሃን መሰረተ ልማቶች ላይ የባላስቲክ ሚሳኤልና የድሮን ጥቃት እየፈጸመች ነው ያሉት ሀገራቱ፥ ይህንን ድርጊት እንድታቆም መጠየቃቸውን የዘገበው አናዶሉ ኤጀንሲ ነው፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

