Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዓለም ትልቁን የኢራን የጋዝ ማምረቻ እንደሚያወድሙ አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በኳታር ላይ ድጋሚ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በዓለም ትልቁን የቴህራን የጋዝ ማምረቻ ማዕከል በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያጋዩ አስጠንቅቀዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ንብረትን እያወደመ፤ የሰው ሕይወትንም እየቀጠፈ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ኢራን በኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የነዳጅ ማውጫ ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች፡፡

ቴህራን ጥቃቱን የፈጸመችው እስራኤል በደቡብ ፓርስ ውስጥ የሚገኘው የኢራን የተፈጥሮ ጋዝ ማዕከል ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው፡፡

ኢራን በአጸፋዊ ርምጃዋ በተለይም ራስ ላፋን በተሰኘው ግዙፍ የኳታር የተጣራ የተፈጥሮ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ማዕከል ላይ የፈጸመችው ጥቃት ዋሽንግተን እና ዶሃን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡

በተፈጸመው ጥቃት ራስ ላፋን የነዳጅ ማቀነባበሪያ ማዕከል ላይ እሳት ተነስቶ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ኢራን ለቀጣናው ቀውስና አለመረጋጋት ከፍተኛ ስጋት ናት ያለው ሚኒስቴሩ ÷ በዶሃ የሚገኙ የኢራን ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ አታሼዎች ከሀገሪቱ መባረራቸውን ጠቅሷል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ አሜሪካ እና ኳታር እስራኤል በኢራን የጋዝ ማምረቻ ማዕከል ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት ምንም አይነት መረጃም ሆነ ተሳትፎ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም ኢራን በኳታሩ ራስ ላፋን የነዳጅ ማቀነባበሪያ ማዕከል ላይ የፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉ መኮነናቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን በድጋሚ ኳታር ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ አሜሪካ በደቡብ ፓርስ የሚገኘውንና በዓለም ትልቁን የቴህራን የጋዝ ማምረቻ ማዕከል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንደምታወድመው አስጠንቅቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version