አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ማቋቋሚያ ከ35 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዛሬው ዕለት አስረክበዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ሁለት ፒካፕ ተሽከካሪዎችን ድጋፍ ማድረጉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በዞኑ የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የጣለው ከባድ የጎርፍ እና የመሬት ናዳ አደጋዎችን በማስከተሉ በሰዎች ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
በአደጋው ጋጮ ባባ፣ ቦንኬ እና ካምባ ዙሪያ ወረዳዎች እንዲሁም ሌሎች የዞኑ አከባቢዎች ከፍተኛ ጉዳት አስተናግደዋል።
በተለይ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰበት ጋጮ ባባ ወረዳ ማዜ ዶይሳ ቀበሌ ቀደም ብሎ በተከሰተው ናዳ የሞቱትን ሰዎች ለማውጣት ርብርብ እያደረጉ የነበሩ 125 ሰዎች በድጋሚ የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል።
አደጋው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እና የግል ድርጅቶች ለተጎጂዎች የሚያደርጉት ድጋፍም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

