Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከተማዋን የሚመጥን የፀጥታ መዋቅር እንገነባለን- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማን የሚመጥን የፀጥታ መዋቅር እንደሚገነባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከፀጥታ ዘርፍ አካላት እና የክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  ውይይት ማድረጋቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬታሪያት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱም የሰላም እሴቶችን በማበልጸግ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ፣ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ለመከላከል እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነዋሪውን ያሳተፈ የጸጥታ ምክር ቤት ማቋቋም በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር ተደርጓል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስት መቀመጫ፣ የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ የነዋሪዎቿን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ ስራ ነውም ብለዋል

የከተማዋን ሰላም ማረጋገጥ የሚችል ዘመናዊ እና የተቀናጀ አደረጃጀት ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ አዳነች፥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተጀመረው የኮሚዩኒቲ ፖሊስ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version