አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ይገኛል፡፡
በተለይም በቅርቡ የጦርነቱ ተሳታፊ ሀገራት የጥቃት ኢላማቸውን በነዳጅ ማምረቻ ማዕከላት ላይ ማነጣጠራቸውና የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡
ይህን ተክሎም ሀገራት በቀጣናው በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋም የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል፡፡
በዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ቻይና እና ጃፓን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት አይቀሬ የሚመስለውን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋም የተለያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ እና ታይላንድን የመሳሰሉ የእስያ ሀገራትም አስገዳጅ የነዳጅ ቁጠባ ርምጃዎችን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
እንደ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ ከነዳጅ ምርት ጋር ያላቸውን ጥገኝነት በመቀነስ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአማራጭነት እየተጠቀሙ ነው፡፡
ሀገራት በመጀመሪያ ደረጃ የነዳጅ ምርት አቅርቦት ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስ ዜጎች ምርቱን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ አከናውነዋል፡፡
እንደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያሉ ነዳጅን የሚተኩ ሌሎች የሃይል አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነም እያስገነዘቡ ነው፡፡
ለዚህም ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን እንዲገዙ ከቀረጥ ነጻ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረጉ ያሉ ሀገራት መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡
ነዳጅን ለመቆጠብ የሥራ ቀናትን በመቀነስ ሠራተኞች ቤት ሆነው በርቀት እንዲሰሩ ያደረጉ ሀገራት በርካቶች ናቸው፡፡
የሕዝብ ትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም፣ አጫጭር መንገዶችን በብስክሌትና በእግር መጓዝም ነዳጅን ለመቆጠብ ሀገራት ከሚያበረታቷቸው መፍትሄዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የተለያዩ ነዳጅ አምራች ሀገራት ምርቱን ወደ ውጪ መላክ በማቆም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ እንዲውል የወሰኑ ሲሆን÷ ችግሩን ለመቀነስ የአደጋ ጊዜ የነዳጅ ክምችትን የለቀቁ ሀገራት መኖራቸውንም የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል ሀገራት የነዳጅ አቅራቢዎች እና ማደያዎች የየሀገራቱ መንግሥታት ቅድሚያ ለሚሰጧቸው መሠረታዊ ነገሮች ምርቱን ቅድሚያ እንዲሰጡ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በመላኩ ገድፍ

