አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 500 ግራም ኮኬይን አደንዛዥ ዕጽ ደብቃ ለማሳለፍ የሞከረች ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለች።
ሙኪሳ ስቴላ የተባለችው ኡጋንዳዊት ግለሰብ አደንዛዥ ዕጹን በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ውስጥ በረቀቀ መንገድ ደብቃ ለማሳለፍ ስትሞክር በቁጥጥር ስር መዋሏን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዋ ከማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንጌ ተነስቶ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትራንዚት በማድረግ ወደ ፊሊፒንስ ማኒላ በመጓዝ ላይ በነበረ አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍራ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ባለሙያዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በዘመናዊ መሣሪያዎች ባከናወኑት ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር ኮኬይኑ ከነተጠርጣሪዋ በቁጥጥር ስር መዋሉን መረጃው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አደገኛ ዕጽዋት ቁጥጥርና ወንጀል ምርመራ ዘርፍ አደንዛዥ ዕጹን ለተጨማሪ ምርመራ መረከቡን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ በኩል ወደተለያዩ ሀገራት በመጓዝ ላይ በነበሩ አውሮፕላኖች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የተለያየ መጠን ያለው ጫት በቁጥጥር ስር መዋሉም ተመላክቷል፡፡
ከቀናት በፊት ከ4 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወስ ነው፡፡

