Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባዮቴክኖሎጂ ለአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት መሳካት ሞተር ነው – ካኒሺዬስ ካናንጊሬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባዮቴክኖሎጂ ትግበራ ለአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትና መሳካት ዋነኛ ሞተር ነው አሉ የአፍሪካ ግብርና ቴክኖሎጂ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ካኒሺዬስ ካናንጊሬ (ዶ/ር)።

ዋና ዳይሬክተሩ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ባዮቴክኖሎጂን በዘርፉ ተግባራዊ ማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን፣ ድርቅን፣ ተባዮችንና ዝቅተኛ ምርታማነት ለመዋጋት ባዮቴክኖሎጂ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን ገልጸው፥ በአህጉሪቱ በዘርፉ ውጤታማ ተሞክሮዎች እየታዩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለአብነትም በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በኢትዮጵያ በበቆሎ እና ጥጥ ዙሪያ በተሰሩ የባዮቴክኖሎጂ ምርምሮች ከፍተኛ ውጤቶች መምጣታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ በርካታ ተመራማሪች መኖራቸውን አድንቀዋል።

አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች  የአፍሪካን ግብርና በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ አቅም ቢኖራቸውም በህዝቡ ዘንድ የመረጃ ክፍተትን ለመሙላት የብዝሃ አካላት የተቀናጀ ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ፋውንዴሽኑ አፍሪካውያን በቴክኖሎጂው እንዲተማመኑ የሚያስችል ግንዛቤ በመፍጠር ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብርናን ለማህበረ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሞተር ለማድረግ፣ የራሳችንን ለውጥ በራሳችን በገንዘብ መደገፍ ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

የምግብ ስርዓቱን ከውጭ በሚመጣ ድጋፍ ብቻ በመመርኮዝ በዘላቂነት ማሳደግ አይቻልም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በአሁኑ ጊዜ የምንኮራባቸው አብዛኞቹ ለውጦች በበጎ አድራጊዎች የተቸሩና ከውጭ አጋሮች የተገኙ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የምርምር ተቋማቱ ባዮቴክኖሎጂን አፍሪካዊ በማድረግ የአህጉሪቱ የግብርና ዘርፍ ችግሮች እንዲፈቱ መስራት ይገባልም ብለዋል።

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version