አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከነዳጅ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በነዳጅ ስርጭት ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ 14 ተጠርጣሪዎችን መዝገብ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት 1ኛ ተጠርጣሪ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚን አቶ እስመለዓለም ምህረቱ፣ 2ኛ የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ ዘርፍ ም/ዳይሬክተር ዲባራ ፉፋ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በየክፍለ ከተማው በንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ የነዳጅ ቁጥጥር ቡድን መሪና ባለሙያዎችን ጨምሮ አጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ተመላክቷል።
በዚህም መርማሪ ፖሊስ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ተገቢ ያልሆነው ጥቅም ለራስ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ መንግስት በከፍተኛ ወጪ በድጎማ የሚያቀርበውን ነዳጅ ከመመሪያና ከደንብ ውጪ በማሰብ ነዳጁን ለማይመለከታቸው አካላት ያለአግባብ እንዲሰራጭ በማድረግ በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል የመንግስት ተቋማትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ክ/ከተሞች በኃላፊነት ተመድበው በመስራት ላይ እያሉ መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ወደ ሀገር የሚያስገባዉን ነዳጅ ከተለያዩ የነዳጅ አስመጪ ኩባንያዎች፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ከሚገኙ የክልል ነዳጅ ማደያ ባለቤቶችና የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች እና ህገ ወጥ ደላሎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ለታለመለት ዓለማ እንዳይዉል አድርገዋል በማለት የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሆን ብለው ነዳጅ የሚያጓጉዙ ቦቴ መኪናዎች ወደ ነዳጅ ማደያ ስፍራ ገብተዉ እንዳያራግፉና መንግሥት ታሪፍ እስከሚጨምር እንዲቆዩ በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ ተመልሶ ከሀገር እንዲወጣ በማድረግ መንግሥት በቂ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ ባለበት ሁኔታ ሆን ብለዉ ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር በማድረጋቸዉ በደረሰው ጥቆማ መነሻ በቁጥጥር ስር አውሎ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ለችሎቱ አስታውቋል።
መርማሪ ፖሊስ 1ኛ ተጠርጣሪ እስመዓለም ምህረቱን በሚመለከት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነዉ በመስራት ላይ እያሉ ለጊዜው በቁጥጥር ስር ካልዋሉ ግለሰቦች ጋር በመቀናጀት ከኩባንያዎች እና ማደያዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር የነዳጅ ምርት ከተባለው መዳረሻ ውጭ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ እንዲወጣና በኮንትሮባንድ መንገድ እንዲሽጥ ማድረጋቸውን ጠቅሷል፡፡
በዚህም በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ነዳጅ የጫኑ 68 ቦቴዎች (33 በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እና 35 በግል ኩባንያዎች የተጫኑ) እንዲሰወሩ አድርጓል የሚል የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
2ኛ ተጠርጣሪ ዲባራ ፉፋን በሚመለከት ደግሞ የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ ዘርፍ ም/ዳይሬክተር ሆነዉ በመስራት ላይ እያሉ ኃላፊነቱን ሽፋን በማድረግ በኢንቨስትመንት ሽፋን በቀጥታ ተጠቃሚነት ተመዝግበው ነዳጅ ለሚሰጣቸውና ኢንቨስትመንታቸው ለተቋረጠ፣ ፈቃድ ያልወሰዱ እና ስራ ያጠናቀቁ 800 የሚሆኑ አካላት ነዳጅ ያለገደብ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል የሚል የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አቅርቧል።
በኮንትሮባንድ መንገድ ነዳጅ ጭነው ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ አባላት የተያዙ ቦቴዎችን የህጋዊነት ደብዳቤ ሽፋን በመስጠት እንዲለቀቁ አድርጓል በማለት ለችሎቱ የምርመራ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
በተጨማሪም መንግሥት ግንባታቸው ለተጠናቀቁ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ መስጠቱን እንደሽፋን በመጠቀም አዲስ ለሚከፍቱ የማደያ አገልግሎት እኛ ነን ያስፈፀምነው በሚል እስከ 5 ሚሊየን ብር ድረስ በመቀበል ፍቃድ እንዲያገኙ አድርጓል።
መርማሪ ፖሊስ ከተራ ቁጥር 3 እስከ 14ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተጠርጣሪዎችን በተመለከት ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ክ/ከተሞች ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ተመድበው ሲሰሩ የነዳጅ ምርት ለተጠቃሚው በህጋዊና በዲጂታል አሰራር መሸጡን የመከታተልና የማረጋገጥ ኃላፊነቱን በመተው ከነዳጅ ማደያዎች ጋር የጥቅም ትስስር ፈጥረዉ የነዳጅ ምርት በህገ ወጥ መንገድ ከቦታ ወደ ቦታ እንዲዘዋወርና በኮንትሮባንድ እንዲሸጥ በማመቻቸት ለድርጊቱ ፈጻሚዎች ሽፋን ይሰጣሉ የሚል የሙስና ወንጀል የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስ የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል በሚል ወር በገባ ከ24 ጀምሮ ምርት የሚሰውሩና በኮንትሮባንድ የሚሸጡ ማደያዎች በህግ እንዳይጠየቁና ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት እንዲከሰት እንደሚያደርጉ አመልክቷል፡፡
የነዳጅ ሽያጭ በህጋዊ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት እንዳይፈጸም በማድረግ ከታህሳስ 30 እስከ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ከ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ነዳጅ በኮንትሮባንድ እንዲሸጥ በማድረግ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር፣ መንግሥት ገቢ እንዲያጣና የገንዘብ ዝውውሩ ከፋይናንስ ስርዓት ቁጥጥር ውጪ እንዲሆን ያደርጋሉ በማለት ለችሎቱ አብራርቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ህገወጥ ሰርኩላር ደብዳቤዎችን በመፃፍ ከአዲስ አበባ ነዳጅ ጭነው ወደ ክፍለሀገር የሚሄዱ ከባድ ተሸከርካሪዎች ነዳጅ እንዳይሸጥ በማድረግ መጉላላት እየፈጠሩ የሚገኙ መሆኑን ጠቅሶ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ማከናወኛ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ምንም አይነት ወንጀል አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በመከራከር የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቀዋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ ከጀመረው ምርመራ ስራ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መስጠት አስፈላጊነትን በማመን የ12 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ

