አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በጋሞ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች 100 ኩንታል እህል ድጋፍ አድርጓል።
በዕዙ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ኃላፊ ኮሎኔል ለቺሳ መገርሳ እንዳሉት÷ በጋሞ ዞን በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አደጋ የእዙን አባላትና አመራሩን በእጅጉ አሳዝኗል።
ዕዙ ለተጎጂዎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እንዲሆን በዕዙ እርሻ የተመረተ 100 ኩንታል በቆሎ መለገሱን ገልጸዋል።
በቀጣይ ተጎጂዎችን በዘላቂነት በማቋቋም ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ዕዙ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
በተመሳሳይ የጋሞ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሠራተኞችና አመራሩ 126 ሺህ 500 ብር ጥሬ ገንዘብና 255 ሺህ ብር የሚገመት አልባሳትና የቤት መስሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ አመራርና ሰራተኞች እንዲሁ 61 ሺህ 400 ብርና 30 ሺህ ብር የሚገመት አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁስ በድጋፍ ለግሰዋል።
ከዳሎል ማዕከላዊ ዕዝና ከተለያዩ አካላት የተደረጉ ድጋፎችን የተረከቡት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) የዕዙ አባላትና አመራሮች ተጎጂዎችን ለማፅናናትና አለኝታነታቸውን ለመግለጽ ድጋፍ ይዘው በመምጣታቸው አመስግነዋል።
በዞኑ በጋጮ ባባ እና ሌሎች ወረዳዎች በደረሰ የተፈጥሮ አደጋ በርካታ ወገኖች መጎዳታቸውን ገልጸው÷ ከሁሉም አቅጣጫ በርብርብ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ወገኖችን ለማቋቋም ፋይዳው የጎላ በመሆኑ እንዲጠናከር ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

