አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ከፈረንጆቹ 1980 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኖርውዝ ፌስቲቫል በመባል የሚታወቀውን የፐርሺያ አዲስ ዓመት ጦርነት እያካሄደች ባለችበት ወቅት እያከበረች ነው፡፡
21ኛ ቀኑን የያዘውና አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት የመካከለኛው ምስራቅ ጦሪነት ዛሬም የቀጠለ ሲሆን÷ እስራኤል የአየር ድብደባን በቴህራን እንዲሁም ኢራን በምላሹ በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ እየሩሳሌም አስወንጭፋለች፡፡
ኢራን የዘንድሮን የፐርሺያ አዲስ ዓመት እያከበረች የምትገኘው ጦርነት እያካሄደች ሲሆን÷ የኖርውዝ ፌስቲቫል ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ እየተከበረ የዘለቀና ኢራናዊን ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን እና ብሔራዊ ማንነታቸውን የሚገልጹበት በዓል እንደሆነም ይነገራል፡፡
ሆኖም ግን ሀገሪቱ ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር እያካሄደች ባለው ጦርነት ምክንያት እንደ ሌሎች ጊዜያት ደማቅ በዓል መሆን አልቻለም፡፡
በርካታ መሪዎቿን የተነጠቀችው ኢራን አሁንም ጦርነቱን የቀጠለች ሲሆን÷ ከእስራኤል በተጨማሪ ሚሳኤሎቿንና ድሮኖችን ወደ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ባህሬን ማዝነቧን ቀጥላለች፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከኢራን የተተኮሱ አራት ባላስቲክ ሚሳኤሎችና 26 ድሮኖች ማክሸፉን አስታውቋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ ከኢራን የተተኮሱ 27 ድሮኖች ማምከኗን ይፋ ያደረገች ሲሆን÷ ኩዌት እና ባህሬንም በኢራን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢራን ብሪታኒያ ወታደራዊ ይዞታዋን አሜሪካ አንድትጠቀም ከፈቀደች በጦርነቱ እንደተሳተፈች እንቆጥረዋለን ብላለች፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጣ ትዕዛዝ በኢራን የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ የምናደርገውን ጥቃት ለጊዜው አቁመናል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይና ምክትል ሕዝብ ግንኙነት አሊ ሞሃመድ ናኢኒ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃቶች መገደላቸው ተገልጿል። አሊ ሞሐመድ ናኢኒ የአብዮታዊ ዘቡን ለአራት አስር ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ቃል አቀባይ በመሆን መስራታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።
በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳው ጦርነት የፐርሺያ አዲስ ዓመትን ጨምሮ የዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር ላይ ጥቁር ጥላ አጥልቶበታል።
በአቤል ነዋይ

