አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሊተላለፍ የነበረ 40 ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ባለሙያች በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ እንዳመለከተው÷ ከታይላንድ ባንኮክ ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ መዳረሻው የሆነ አውሮፕላን በአዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትራንዚት ሲያደርገ በረቀቀ መልኩ በሻንጣ ውስጥ የተደበቀ 37 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የእንግሊዝ ዜግነት ያለው የአደንዛዥ ዕጹ አዘዋዋሪም ተይዞ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ከፈረንሳይ ፓሪስ ወደ ኮሞሮስ ዋና ከተማ ሞሮኒ ሲጓዝ በነበረ አውሮፕላን ላይ በሻንጣ የውስጥ አካል ላይ በረቀቀ መልኩ የተደበቀ 3 ነጥብ 160 ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በትራንዚት በኩል ለማሳለፍ ሲሞከር በቁጥጥር ስር መዋሉም ተገልጿል፡፡
አደንዛዥ ዕጾቹ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ በተዘረጋው ግልጽ የአሰራር ስርዓት አማካኝነት ከባለድርሻ አካላት ጋራ በመቀናጀት እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በተከናወኑ ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር መያዛቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡
በተከታተይ ቀናት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አደንዛዥ ዕጽ ለማስተላለፍ ሲደረጉ የነበሩ ሙከራዎች እንደወትሮው ሁሉ በሚከናወኑ ጥብቅ ፍተሸና የቁጥጥር ሥርዓቶች አለመሳካታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውሷል።
የሀገርን ብሔራዊ ደኅንነትና የኢትዮጵያ አየር መንገድን መልካም ስምና ገጽታ የሚጎዱ መሰል ወንጀሎችን በከፍተኛ ዝግጁነትና በተደራጃ መንገድ የመከላከል እምጃዎቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጧል፡፡

