አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል አሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በሀገራዊ ጥቅም፣ በሙያዊ ስነ ምግባር እንዲሁም ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ዙሪያ ያሰለጠናቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችን አስመርቋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገር እንዳትዳከም ማድረግ የሚቻለው በአንድነት መቆም ሲቻል ነው ብለዋል።
ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ዜጎች ለብሔራዊ ጥቅም መከበር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበው፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅም ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ በባለስልጣኑ የልህቀት ማዕከል ጋዜጠኞች ስልጠና ማግኘታቸውን አንስተዋል።
ጋዜጠኞቹ ከተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለብሔራዊ ጥቅም መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በዙፋን አምባቸው

