አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሹዋሊድ ክብረ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል አለ የሀረሪ ክልል።
የሀረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ከቀናት በኋላ የሚከበረውን የሹዋሊድ ክብረ በዓልን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ክብረ በዓሉ በሀረሪ ብሔረሰብ ዘንድ ለምዕተ ዓመታት ሲከበር የኖረ ነው።
በዓሉ በትውልድ ቅብብሎሽ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ ከነክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ እንደሆነ አመልክቷል።
ዘንድሮ “ሹዋሊድ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር ገልጿል።
በዓሉ ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ጠቁሟል።
በበዓሉ በሀረር ከተማ የባህል፣ ፌስቲቫል እና አውደ ርዕይ፣ የልማት ስራዎች ጉብኝትን ጨምሮ ሌሎች መርሐ ግብሮች ይከናወናሉ።
በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የሹዋሊድ በዓል አከባበር ከሕዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።
የአብሮነት ዕሴትን እያጎለበቱ ከሚገኙ ባህላዊ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን በተለይም በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የባህል ትውውቅ በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በዓሉ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃርም የላቀ ጠቀሜታ አለው።

