Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ2 ነጥብ 32 ቢሊየን ብር የተገዙ የግብርና መሳሪያዎች ለክልሎች ተሰራጩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት አጋሮች ድጋፍ በ2 ነጥብ 32 ቢሊየን ብር ወጪ የተገዙ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ለክልሎች አስረክቧል፡፡
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የግብርና ዘርፉን እድገት ይበልጥ ለማሳለጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
ዘርፉ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር የተሻለ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
ድጋፉ ግብርናን ለማዘመን፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ጥራትን በማስጠበቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለክልሎች ከተሰራጩት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች መካከል 63 ትራክተሮች፣ 71 ወኪንግ ትራክተሮች፣ 150 የሩዝ ማቀነባበሪያ ማሽኖች፣ 4 ባለብዙ ደረጃ እንቁላል መታቀፊያዎችና 5 የከርሰ ምድር ውሃ ማውጫ ማሽኖች ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም 460 በፀሃይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች፣ 15 የመስክ መገልገያ መኪኖች፣ 243 ሞተር ሳይክሎች እንዲሁም 980 ዴስከቶፕ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች መሰራጨታቸው ተመላክቷል፡፡
በሳራ ስዩም
Exit mobile version