Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ የሆነው የሀምበሪቾ 777 ደረጃዎችና 777 መረማመጃዎች…

‎አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከከምባታ ሕዝብ ታሪክ ጋር የተያያዘው ሀምበርቾ ተራራ ከአዲስ አበባ 260 ኪሎ ሜትር፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ዱራሜ ደግሞ በ8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝና 777 የመወጣጫ ደረጃ የተሰራለት ተራራ ነው።

የተራራው መወጣጫ ደረጃዎች ከሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሲሆን÷ ሰባት ተራራዎች አንድ ላይ መሆናቸውን፣ ከተራራው የሚፈልቁ ሰባት ምንጮች ሄደው አንድ ወንዝ መፍጠራቸውን እንዲሁም ሰባት ቀደምት የብሔረሰቡ ጎሣዎች በቦታው ላይ መስፈራቸውን ለማመላከት 777 ደረጃዎች መሰራታቸውን ተመላክቷል።

በዚህም እጅግ ውብ ተፈጥሮን የታደለውና ከባሕር ጠለል በላይ 3 ሺህ 58 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ሀምበሪቾ ተራራ በአካባቢው ከሚኖረው ማሕበረሰብ ጋር እጅግ የተቆራኘ መሆኑን ይገለጻል።

ቀደም ባለው ጊዜ ወደ ተራራ ለመውጣት ሰዎች እንደሚቸገሩና ከ2012 ዓ.ም ወዲህ በተሰራው 777 መወጣጫ ሕብረተሰቡ ተራራውን በመውጣት ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም የተራራው 777 መወጣጫ ጨርሰው ተጨማሪ 300 ሜትር ያህል ጎብኝተው እንደተመለሱ አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመለከቱትን የተፈጥሮ ደን፣ ተራራው አናት ላይ ያለውን አረንጓዴና ሜዳማ ስፍራ እንዲሁም ተጨማሪ ማራኪ ስፍራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን በመጥቀስ÷ የተሰሩ 777 መወጣጫዎች እነዚህን የመሳሰሉ ድንቅ ቦታዎች ለመጎብኘት በቂ ባለመሆናቸው ተጨማሪ መወጣጫ ደረጃዎች እንዲሰሩ ሐሳብ መስጠታቸውን አመላክተዋል።

በዚህም መነሻነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ለስራው የሚያስፈልግ ግብዓትና በጀት ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር የዞኑ ሕዝብ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ተጨማሪ የመወጣጫ ደረጃዎች መስራት ተጀምሮ በሶስት ወር ጊዜ ተጠናቅቋል።

በተሰራው ስራ ተጨማሪ 777 ደረጃዎች እንዲሁም 777 መረማመጃዎች ተሰርተው አጠቃላይ ደረጃዎቹና መረማመጃዎቹ ሦስት 777 መድረሳቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ከዚህ በፊት ለመድረስ አዳጋች የነበረውን የሀምበሪቾ ተራራ መጨረሻ በመወጣጫ ደረጃዎች ሰው ሳይቸገር መድረስ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

አዲስ በተከናወነው የተራራ ልማት ቀደምት የከምባታ ሕዝብ አስተዳደርን (ሰጄ አስተዳደር) የሚያሳይ የቱሪስት መስህብ ስራ እንዲሁም ቀደምት የከምባታ መሪዎች መሃላ የሚፈጽሙበት “የኪዳን/መሃላ ድንጋይ (ህድር ክኒ)” ታሪካዊ ስፍራ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ጉብኝት ወቅት በድንገት ተገናኝተው በሽማግሌ የተመረቁበት ሥፍራ “ማሰ  ክኑ” ምቹ የቱሪስቶች መስህብ የማድረግ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ስራው ከተከናወነ በኋላ በስፍራው በመገኘት በተሰሩ ስራዎች ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ስራውን ለማከናወን በጥሬ ብር ወጪ የተደረገውን 16 ሚሊየን ብር ለመስጠት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

በሰው ኃይል በተከናወነው የተራራ ልማት ወጣቶችን ጨምሮ የአካባቢው ሕብረተሰብ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉ ተገልጿል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version