Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአርሶ አደሮች የሚሰጠውን ዲጂታል የብድር አገልግሎት ለማጠናከር..

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብርና ሚኒስቴር እና አዋሽ ባንክ ለአርሶ አደሮች ዲጂታል የብድር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ለዚህም አዋሽ ባንክ አርሶ አደሮች ዲጂታል የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል “አዋሽ ኢ ፋርም” የተሰኘ የዲጂታል ሥርዓት ማበልጸጉ ተመላክቷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ የፋይናንስ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል፡፡

በዘርፉ ያለው የብድር ተደራሽነት 10 በመቶ እንደማይደርስ ጠቁመው÷ አዋሽ ባንክ የጀመረው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአርሶ አደሮች የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የአዋሽ ባንክ ቺፍ ማርኬቲንግ ኃላፊ ዮሐንስ መርጋ በበኩላቸው÷ አዋሽ ባንክ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት በፋይናንስ ዘርፉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባንኩ አዋሽ ኢ ፋርም የተሰኘ የዲጂታል ሥርዓት በማበልጸግ አርሶ አደሮች ዲጂታል የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

አገልግሎቱ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና ሌሎች ግብዓቶችን በቀላሉ ማግኘት ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version