Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመዲናዋን የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የሚመጥን ደንብ ማስከበር ለማከናወን…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን የሚመጥን ደንብ ማስከበር ለማከናወን አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል አለ የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለፋ ዲጂታል እንዳሉት ÷ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ከተማዋን ውብ፣ ዘመናዊ እና ለኑሮ ምቹ አድርገዋል፡፡

ይህም የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪስት መዳረሻነት እና የኮንፈረንስ ማዕከልነት ይበልጥ እያጠናከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ የደረሰችበትን እድገትና ደረጃ የሚመጥን የደንብ ማስከበር ሥራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካትም በዲሲፕሊን የታነጸና ነባራዊ ሁኔታውን የሚገነዘብ አመራርና የደንብ ማስከበር ኦፊሰር ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

 


የባለስልጣኑ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በበከሉቸው÷ የደንብ ማስከበር ሥራዎችን በማሳለጥ አዲስ አበባን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ከተማ የማድረጉ ሒደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመሬት ወረራ፣ በሕገ ወጥ ንግድ፣ በአዋኪ ተግባራትና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የደንብ ጥሰቶችን ለመከላከል በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው ÷ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል አመራሩ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በደንብ ማስከበር ሥራ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቆጣጠር ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

በሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን የታነጹ፣ በቀናነት ሕብረተሰቡን የሚያገለግሉ አመራሮችን እና ፓራ ሚሊተሪ ኦፊሰሮችን የማፍራቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከወረዳ እስከ ማዕከል ለሚገኙ አመራሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባን ውበት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሕብረተሰቡ ከአመራሩና ኦፊሰሮች ጋር በትብብር በመስራት የደንብ ጥሰቶችን እንዲከላከልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version