አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ወጣቶች አፍሪካን የሚያነቃ እምቅ አቅም አላቸው አሉ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም ውይይት ማህበር፣ ከኢንተርኮንቲኔንታል ዩዝ ኮኔክት እና ከሌሎች አህጉራዊ አጋሮች ጋር በመሆን ነው ያዘጋጀው 6ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የዲፕሎማሲ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
“ከፖሊሲ ወደ ተግባር፤ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት በአፍሪካውያን የሚመሩ መፍትሄዎችን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ፖሊሲ አውጪዎች ተገኝተዋል።
የጉባኤው ዋና ዓላማ ወጣቶች በአህጉራዊ የሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚ ውህደትና በፈጠራ ስራዎች ላይ ያላቸውን ሚና ወደ ላቀ ተግባራዊ ደረጃ ማሸጋገር እንደሆነ ተገልጿል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ወጣቶች አህጉሪቱን ከችግር የሚያወጣ እና የሚያነቃ እምቅ አቅም አላችሁ ብለዋል።
የአፍሪካን ዕድገት በጋራ ማፋጠን እንደሚገባም አስገንዝበው፤ የአፍሪካ የእድገት አጀንዳ በማስቀጠል ረገድ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አመላክተዋል።
ዓለም ወደ ዲጂታል እየተቀረ ባለበት ሁኔታ አፍሪካውያን ወጣቶች በዘርፉ ላይ በተለይም እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላሉት ዕውቀቶች ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የምንፈልጋትን አፍሪካ በጋራ እንገነባለን ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለወጣቶች ምቹ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የሥራ ከባቢን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
ዕውቀትን ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር በማቀናጀት ከንግግር ባለፈ ወጣቶች መሪ የሚሆኑበትን እውነተኛ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ወጣቶች የቀደሙ ትውልዶችን ጥበብ በመጠቀም የምንመኛት አፍሪካን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በሶስና አለማየሁ

