አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዲስ አበባ መሬት አስተዳደር የዲጂታል ካርታ ለማስወጣት ለአመራሮች የሚከፈል በሚል በሀሰተኛ ሰነድ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በመቀበል በከባድ ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 5 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች ዳዊት መንግስቱ፣ ሳሙኤል ኪዳኔ፣ ቶማስ ማናዬ፣ ፅዮን አበራ እና ሚኪያስ አውላቸው ናቸው።
ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ዝርዝር እንዳመላከተው፤ ተከሳሾች በየካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም አንድ የግል ተበዳይን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ውስጥ ባለው 3 ሺህ 825 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ይዞታው ላይ ከአርሶ አደር ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ወደ ዲጂታል ካርታ ቀይሮ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለማውጣት በሂደት ላይ እያለ 1ኛ ተከሳሽ የራሱ ይዞታ ላይ ዲጂታል ካርታ እና የኢንቨስትመንት ፍቃድ እንዳወጣና ከመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊና ባለሙያዎች ጋር ቅርበት ያለው መሆኑን ጠቅሶ ለኃላፊና ለባለሙያዎች የሚከፈል እና ለተለያየ ወጪዎች በማለት የማስማማት ስራ መስራቱ በክሱ ላይ ተመላክቷል።
በሌላ ቀን ደግሞ ለግል ተበዳይ 2ኛ ተከሳሽ ስሙ በረከት እንደሚባልና የከተማ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ባለሙያ እንደሆነ፤ 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የኃላፊ ሹፌር እንደሆነ አድርጎ ያስተዋወቀው መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል።
በዚህ መልኩ ትውውቅ ካደረጉ በኋላ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾቹ 1ኛ ተከሳሽ ባስተዋወቃቸው አግባብ የተቋማቱ ሰራተኞች መሆናቸውን በመግለፅ ለግል ተበዳይ በጋራ እና በተናጠል በተለያየ ጊዜ ስልክ በመደወልና በአካል በማግኘት የዲጂታል ካርታው እየተሰራለት በሂደት ላይ ያለ መሆኑን የጠቀሱና ለጉዳይ ማስፈጸሚያ በሚል በተለያየ ጊዜ ገንዘብ እንዲያስገባ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም “መኮንን ያያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬትና ልማት ቢሮ ኃላፊ በሚል ሀሰተኛ ቲተርና ክብ ማህተም ያለበት የሲዲ የካርታ ቁጥር የተጠቀሰበትን ሀሰተኛ ደብዳቤ “እንኳን ደስ አለህ ጉዳዩን ተጨርሷል ” በሚል 1ኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ ሰነድ ለግል ተበዳይ የሰጠ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
በዚህ መልኩ የግል ተበዳይ 6 ሚሊየን 239 ሺህ 946 ብር እንዲያስገባ የተደረገና በተለያዩ ጊዜ በተለያዩ መጠኖች ገንዘቡን ለ4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ማስተላለፉና መጠቀማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አመልክቷል።
ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾችን የተሳትፎ ደረጃ ዘርዝሮ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የማታለል ወንጀል እና መንግታዊ ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት፣ ወደ ሀሰት መለወጥ ወይም በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሚል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በሌላኛው ክስ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተብሎ በሚጠራበት አከባቢ ሌላ የግል ተበዳይን የነበራቸውን 49 ሺህ 500 ካሬ ሜትር የአርሶ አደር ይዞታ ማረጋገጫ ካርታቸውን ወደ ዲጂታል ካርታ ቀይሮ በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ለማልማት በአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በሂደት ላይ እያሉ ተከሳሽ በአካባቢው ላይ የግል ትውውቃቸውን መሰረት በማድረግ የማታለል ወንጀል መፈጸሙን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።
በዚህም ተከሳሹ የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ “የራሱን ዲጂታል ካርታ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊና ባለሙያዎችን ስለማውቃቸው ቶሎ አስጨርሻለው የአንቺንም አስጨርስልሻለው” በማለት በማታለል ለኃላፊዎች የሚከፈል ጉዳይ ማስፈጸሚያ በሚል 270 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቡ እንደተላለፈለት ተጠቅሷል።
ከዚህም በኋላ በግል ተበዳይ ስም የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በሚል የተዘጋጀ ዲጂታል ካርታ የሚመስልና ሀሰተኛ ሰነድ የላከላቸው በመሆኑ በክስ ዝርዝሩ ተጠቅሶ የአታላይነት ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት የክስ ዝርዝሩ ለተከሳሾች እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ተዘጋጅተው ለመቅረብ እንዲችሉ በጠየቁት መሰረት ለመጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ

