አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የነዳጅ ብክነትን ለመቀነስ የተቀመጡ የቁጠባ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በክልሉ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተዘጋጀ የነዳጅ ምርት አቅርቦትና ሥርጭት ሥርዓት ለማሻሻል የሚያስችል ክልላዊ የማስፈጸሚያ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
አቶ አወል አርባ በዚሁ ወቅት የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ፍጹም ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ሊመራ እንደሚገባ ገልጸው÷ የነዳጅ ምርት ለክልሉ ልማትና ለሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው አለመረጋጋት በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሕዝብ እንዳይስተጓጎል መንግስት ተገቢውን ክትትልና ርምጃ እንደሚወስድ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
የነዳጅ ብክነትን ለመቀነስና የተቀመጡ የቁጠባ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አንስተው÷ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና አስፈጻሚ አካላት የተቀናጀ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
የማስፈጸሚያ ሰነዱ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማደያዎችና አከፋፋይ ተቋማት ላይ በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲገባና የሥራ አፈጻጸሙም በየጊዜው እንዲገመገም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም ሀገራት የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
መንግስት ከወሰነው የነዳጅ ታሪፍ በላይና ከግብይት ሰንሰለት ውጪ የሚሸጡ ማደያዎች ላይ መንግስት ርምጃ እየወሰደም ይገኛል፡፡

