አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ጦርነቱ እንዲቆም ከአሜሪካ ጋር ንግግር መጀመሯን ለማመን ከብዷታል አሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፡፡
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ እንዳሉት÷ቴህራን በፕሬዚዳንት ትራምፕ በኩል ጦርነቱን ለማስቆም የቀረበውን የመነሻ ሃሳብ ውድቅ በማድረግ የራሷን ቅድመ ሁኔታ ይፋ አድርጋለች፡፡
ኢራን አሁን ላይ ምንም አይነት የመደራደር ፍላጎት የላትም ያሉት ሚኒስትሩ ÷ እራሷን ለመከላከል የምትፈጽመውን ጥቃት ግን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
የሚኒስትሩን ምላሽ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰጡት አስተያየት÷ ኢራን ጦርነቱን ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአሜሪካ ጋር ንግግር መጀመሯን ለማመን ፈርታለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቴህራን በጉዳዩ ላይ ከዋሺንግተን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ንግግር እደረገች መሆኑን ጠቁመው÷ ባለፉት ሶስት ቀናትም በጉዳዩ ላይ ውጤታማ ውይይት መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
ይሁን እንጂ የዓለም ስጋት የሆነውን የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሀገራቱ የንግግር ሒደት አሁንም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በንግግሩ ዙሪያ ቴህራን እና ዋሺንግተን የሚያወጡት እርስ በርሱ የተጣረሰ ሃሳብ የሀገራቱን አለመተማመንና ለንግግር ያላቸው ቁርጠኛነት አነስተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመካከለኛው ምስራቅ ተጠናክሮ የቀጠለው ጦርነት የሰው ሕይወትን እንዲሁም በርካታ መጠን ያለው ንብረትን እያወደመ ይገኛል፡፡
ኢራን በቀጣናው የአሜሪካ ጦር ሰፈር መገኛ በሆኑ ሀገራት ላይ የምትፈጽመውን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ከኢራን የተፈጸሙ የባላስቲክና የድሮን ጥቃቶችን በአየር መቃወሚያ ማክሸፍን አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት እልባት ካልተበጀለት ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ጦርነቱን በንግግር ለመቋጨት ተፋላሚ ወገኖች ብሎም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

