Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ጉዞ አብዮት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም በአየር ብክለትና በነዳጅ ወጪ እየተፈተነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በብዛት ወደ ትራንስፖርት ዘርፉ በማስገባት የአረንጓዴ ሽግግር ጉዞዋን ከጀመረች ሰነባብታለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የትራንስፖርት ዘርፍ የካርቦን ልቀት ከጠቅላላው የአየር ብክለት 24 በመቶ ድርሻ እንዳለው የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ ከትራንስፖርት ዘርፍ የካርቦን ልቀት 90 በመቶ የሚሆነው ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ ሲሆን በተለይም የጭነት ተሽከርካሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ብክለት ያስከትላሉ።
የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ደግሞ ከዚሁ ዘርፍ የካርቦን ልቀት 63 በመቶውን ድርሻ ይዛለች።
ኢትዮጵያ ይህንን ለመቅረፍና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓትን ለመዘርጋት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ማሳደግ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ማጠናከር፣ ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ ማድረግ እንዲሁም የታዳሽ ኃይል ወጪን መቀነስ ከስትራቴጂው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በዚህም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ለመተካት እየተሰራ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ከ100 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ።
እንዲሁም ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በተለያዩ ከተሞች የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡
መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ኩባንያዎች ከቀረጥ ነፃ መብትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ማበረታቻዎችና የኢንቨስትመንት ድጋፎችን በማድረግ ላይ ነው።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ፍላጎቷን በውሃ ሀብቷ የምትጠቀም ሲሆን፥ የታዳሽ ኃይል አቅሟ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች የተሻለ ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
በተጨማሪም ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ በሀገር ውስጥ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለትራንስፖርት ዘርፍ እንድታውል ያስችላታል።
በአጠቃላይ ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአረንጓዴ ጉዞ ሽግግር ውስጥ ያላትን የመሪነት ሚና የሚያሳይ ነው።
በፈረንጆቹ 2024 በዓለም ዙሪያ ከ17 ሚሊየን በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተሸጡ ሲሆን፥ ይህም በቀን ከ1 ሚሊየን በርሜል በላይ የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ ያስቻለ ነው።
በሶስና አለማየሁ
Exit mobile version