አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት የሚገኘውን ገቢ የሀገሪቱ የንግድ ማሕበረሰብ በጥንቃቄ እንዲይዘውና እንዳያባክን አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሞስኮ በተካሄደው የሩሲያ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ስራ ፈጣሪዎች ሕብረት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው ይህንን ያሉት።
የኤክስፖርት ምርቶች ዋጋ በሚጨምርበት ወቅት የሚገኘው ትርፍ እንዳይባክን ያስጠነቀቁት ፑቲን÷ የገበያው ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ ሊቀያየር ስለሚችል ጠንቃቃ የበጀት ፖሊሲ መከተል ይገባል ብለዋል።
አሜሪካ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ አለማንሳቷን ጠቅሰው÷ ተጭነው በባሕር ላይ ለሚገኙ የሩሲያ ነዳጅ ምርቶች የ30 ቀናት የገደብ ማቅለያ መስጠቷን አመልክተዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያደረጉ የሚገኙት ጦርነት የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ጉዳት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን መግለፃቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በሶስና አለማየሁ

