Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ክልል የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ በትግራይ ክልል የምክክር ሒደት ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በክልሉ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን እና የሲቪክ ማህበራት ጋር ከ22 በላይ የውይይት መድረኮች በአዲስ አበባና በመቐለ ከተሞች መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ክልልን ለማካተት ቁርጠኛ ሆኖ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የምክክሩ ሒደት በሌሎች አካባቢዎች በነፃነትና አሳታፊ በሆነ መልኩ መካሄዱን ጠቅሰው፤ በትግራይ ክልል ተወካዮች በኩል የሚደረገው የምክክር መድረክ በተመሳሳይ መልኩ የሚካሄድ በመሆኑ ሁሉም አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

Exit mobile version