አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ35 አመቱ የቀደሞው የራፕ ሙዚቀኛ ባሌንድራ ሻህ በዕድሜ ትንሹ የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ ፈፅሟል፡፡
ከሙዚቃ ሙያው ወደ ፖለቲካው ፊቱን ያዞረው ባሌንድራ ሻህ የሚመራው የራስትሪያ ስዋታንትራ ፓርቲ በሀገሪቱ በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ ብልጫ አሸንፏል፡፡
የቀደሞው ራፐር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት የኔፓልን የወደፊት ተስፋ የሚያሳይና ߵአንድ ኔፓልߴ በሚል በለቀቀው ዘፈን የህዝብን ትኩረት አግኝቷል፡፡
ሙዚቃው በተለቀቀ በሰዓታት ውስጥ 2 ሚሊየን ሰዎች ጋር መድረስ የቻለ ሲሆን ይህም በሀገሪቱ የሙዚቃ ታሪክ አዲስ ክስተት ሆኗል፡፡
የቀደሞው ራፐር በዘፈኑ ስንኞች የኔፓል ወጣቶችን በሀገሪቱ የሚስተዋለውን ሙስና እና የማህበራዊ እኩልነት ችግሮችን ሲተች እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡
ለሦስት አመታት የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካትማንዱ ከንቲባ በመሆን ያገለገለ ሲሆን፥ በሀገራዊ ምርጫው ራስትሪያ ስዋታንትራ ፓርቲን በመወከል ተወዳድሮ ማሸነፍ ችሏል፡፡
ባሌንድራ ሻህ በዛሬው እለት ቃለ መሃላ በመፈጸም አምስት ሴቶች የተካተቱበትን ካቢኔ ይፋ ማድረጉን ዘ ዊክ መፅሄት ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ

