አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶማሊ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት ያጎለበቱ የልማት ስራዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በትብብር መስራት ይገባል አለ።
ቢሮው በዚህ ረገድ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርጓል።
የሶማሊ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መሀመድ አደን በምክክሩ ወቅት እንዳሉት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያጎለበቱ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
እነዚህን እና በክልሉ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እየሰራቸው የሚገኙ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ክልሉ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሀብት አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ደረጀ ብሩ በበኩላቸው፤ ሚዲያው ከክልሉ ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር የክልሉን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ስራዎችን በስፋት የሚሸፍን መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በክልሉ ቋሚ ባለሙያ በመመደብ በቅርበት ሆኖ ሁሉን አቀፍ ስራዎች ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ስራ እንደሚያከናውን ገልጸው፤ ክልሉ ለሚዲያው እያደረገው ለሚገኘው ድጋፍ አመስግነዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከሶማሊ ክልል ባለፈ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል አድማሱን በማስፋት ለአድማጭ ተመልካቹ እያደረሳቸው የሚገኙ ስራዎች እያጠናከረ እንደሆነም አመልክተዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአካባቢው ያለው እምቅ ጸጋ የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ያነሱት ደግሞ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር አፈወርቅ መሐሪ ናቸው።
በተስፋዬ ኃይሉ

