Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በወላይታ ሶዶ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ አንድ ሙሉ ቦቲ ናፍጣ ሲያሸሹ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ከተፈቀደ ህጋዊ አሰራር ወጪ በጥቅም ትስስር የአቅርቦት ችግር ለመፍጠር አንድ ሙሉ ቦቲ ናፍጣ ሲያሸሹ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ እንዳሉት÷ መምሪያው ሌሊቱን ባደረገው ክትትልና ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማራውን የነዳጅ ማመላለሻ ቦቲ ከነናፍጣው በቁጥጥር ማዋል ተችሏል።

ናፍጣን በማደያ የተራገፈ በማስመሰል በጥቁር ገበያ ለመቸብቸብ የተዘረጋው የወንጀል ሰንሰለት በፖሊስ ሰራዊቱ እና በሕብረተሰቡ ትብብር ከሽፏልም ነው ያሉት።

በዚህም 50 ሺህ 895 ሊትር ናፍጣ በከተማ አስተዳደሩ መሀል ክ/ከተማ ዳልቦ ቀበሌ ታንቱ ሻንካ ዳልቦ ጀ ኤፍ አም ማደያ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው÷ በዚሁ ማደያ ከቀናት በፊት 600 ሊትር በላይ ቤንዚል በሮቶ ሲቀዳ መያዙን አስታውሰዋል።

በወንጀል ድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ አራት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ሲያዙ ሌሎች ተጠርጣሪዎች እየታደኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ ማሕበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቨዢን ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ምትኩ ማሞ በበኩላቸው÷ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ በነዳጅ ምርቶች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከነዳጅ ማደያዎች ወጪ የሚደረግ ግብይት ለአደጋ የሚያጋልጥና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ ከዚህ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Exit mobile version