አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የምርጫ መወዳደሪያ ማኒፌስቶውን በዛሬው ዕለት አስተዋውቋል።
ማኒፌስቶው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቢመረጥ የሚሰራባቸው የተለያዩ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፤ ቢመረጥ የሚሰራባቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡
በማኒፌስቶው ዜጎች ማህበራዊ ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በፈጣን የእድገት ጎዳና የሚመራበትን ስልት መቀየስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት እና በሙያ የበቃ ወጣትን መፍጠር የሚሉ ጉዳዮችን መያዙ ተገልጿል።
በተጨማሪም ሙስናን ማጥፋት፣ የዜጎች የዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች ማስከበር እና ሌሎች ጉዳዮች በማኒፌስቶው መካተታቸው ተነግሯል።
በማስተዋወቂያ መድረኩ የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፕሬዚዳንት አብርሃም ጌጡ÷ ሀገርን ወደ እድገት እና የሰላም ጎዳና የሚመሩ ጠንካራ ፖሊሲዎችን እና ሀሳቦችን ይዘን መጥተናል ብለዋል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ እናት ፓርቲ እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) ቅንጅት ነው።
በቅድስት አባተ

