Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበርን ከገጠመው የመፍረስ አደጋ ለመታደግ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ድጋፉ የተደረገው የተለያዩ አካላትን በማስተባበር መሆኑን ገልጸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ የተጫዋቹ እና የማህበሩ ብቻ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ አንዱ የከተማችን ጠንካራ ክለብ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን ሀገራችንን እና ከተማችንን የወከለ ታሪካዊ የስፖርት ማህበር ከመፍረስ የመታደግ ኃላፊነት  እንዳለብን እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል።

የስፖርት ማህበሩ ላለፋት 6 ወራት ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።

የስፖርት ማህበሩ የመበተን አደጋ ተጋርጦበት ማየት ስለሌብን ከከተማችን በጀትም ወስነን፣ ለባለሀብቶች ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሰጡን ፈጣን ምላሽ በጥቅሉ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ አስረክበናል ነው ያሉት።

ድጋፍ ላደረጉት ተቋማት በስፖርቱ ቤተሰብ ስም ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባዋ፤ ድጋፍ አስተዳደራችን ክለቡን ከውድቀት ለመታደግ እና ለስፖርት ወዳድ ህዝብ የሰጠው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉንም ባሳተፈ እና በግልፅነት አዲስ ቦርድ መርጦ ከገጠመው ጊዜያዊ ችግር ተላቅቆ ወደ ቀድሞ ጥንካሬውና ዝናው የሚመለስበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆንም ተመኝተዋል።

Exit mobile version