አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ600 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
የቢሮው ም/ሃላፊና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መላኩ ባፋ እንዳሉት ÷ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በስኬት ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ለመርሐ ግብሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች 600 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ለተከላ የሚዘጋጁት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን አቶ መላኩ ለፋና ዲጂታል አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም ፍራፍሬ፣ ሀገር በቀል የደን ችግኞች፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግኞችን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ቡና፣ የአካባቢን ውበት የሚጠብቁና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የዛፍ ዝርያዎች በዝግጅቱ መካተታቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከመርሐ ግብሩ ጋር በተያያዘ ለችግኝ መትከያ ቦታዎች የካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን በማዘጋጀት እና በሌሎች ሥራዎች በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

