አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚወለዱ ሕጻናትን የሚንከባከቡ ተቋማትን ማስፋት ይገባል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡
የዲቦራ ፋውንዴሽን ዓለም አቀፉ የዳውን ሲንድረም ቀንን “ብቸኝነትን በጋራ እንዋጋ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ6ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት አክብሯል።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት÷ ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚወለዱ ሕጻናትን የሚንከባከቡ ተቋማትን ማገዝና ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዜጎች በመሰል የጤና ችግር ተጠቂ ለሆኑ ሕጻናት እና ቤተሰቦች ያላቸውን አብሮነትና አጋርነት ማሳየት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናትን መንከባከብ ከቤሰተብ ጀምሮ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚወለዱ ሕጻናትን ለሚንከባከቡ ተቋማት የሚደረጉ ዲጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ዲቦራ ፋውዴሽንን በማገዝ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ባለድርሻ አካላት የምስጋናና እውቅና መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንም በሚዲያው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ተበርክቶለታል።
በጀማል አሕመድ

