አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት ዓመታት በሀገር ውስጥ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ማዕከላትን ወደ 60 ለማድረስ እየተሰራ ነው አለ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በሪኦ ሀሰን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ከነዳጅ ጥገኝነት ጋር ተያይዞ እየመጡ ካሉ ፈተናዎች ለማምለጥ የዘርፉን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
አሁን ከ100 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጸው÷ በሚቀጥሉት ዓመታት ይህንን ወደ 500 ሺህ ለማድረስ እቅድ ተይዟል ነው ያሉት።
በሀገሪቱ አሁን ላይ 17 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ማዕከላት መኖራቸውንና ወደ 60 ማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ሁሉም የተሽከርካሪ መገጣጠሚያዎች ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያነት እንዲቀየሩ መመሪያ መተላለፉን ተናግረዋል።
የነዳጅ ማደያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ማዕከል እንዲኖራቸው አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው÷ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አቅርቦት ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የገንዘብና ገንዘብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል።
ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች መከልከላቸውንና ሁሉም የመንግስት ተሽከርካሪ ግዥ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግዥ መዞሩን አንስተዋል።
መንግስት ሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከታክስ ነጻ፣ ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ተገጣጥመው ለሚመጡት 15 በመቶ እና በግማሽ ተገጣጥመው ለሚገቡት 5 በመቶ የጉምሩክ ታክስ ማድረጉንም አስረድተዋል።
ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተጠቃሚዎች በአዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ላይ የዋጋ ቅናሽ እንደሚኖርና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አረንጓዴ ሰሌዳ እንዲለጥፉ እንደሚደረግ ገልጸው÷ ይህም በአቅርቦት ላይ የተያዘውን ዕቅድ በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተወሰደ ያለ ማበረታቻ መሆኑን አመልክተዋል።
ከብዙኃን ትራንስፖርት አኳያ ዘርፉ ላይ የመንግስትና የግል አጋርነት በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን÷ የውጭ ባለሃብቶችን በሽርክና ለማሳተፍ ንግግር እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ቀውስ የነዳጅ አቅርቦትን እያስተጓጎለ በመሆኑ መኪና የማሽከርከር ልምድን መቀየር፣ የብዙኃን ትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም፣ የእግር ጉዞና የሞተር አልባ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሳፍንት እያዩ

