አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የአፍሪካ የባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ፌስቲቫል እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
በስምምነቱ መሰረት በተያዘው የፈረንጆቹ 2026 የሚካሄደውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች መልቲ-ኤቨንት ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ይካሄዳል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ መኪዩ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያላትን ጥንታዊና ደማቅ የባህል ስፖርት እሴቶች ከአህጉራዊው እንቅስቃሴ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል ነው፡፡
ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፥ መንግስት የሀገር በቀል ስፖርቶች እንዲያድጉና ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሀመድ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ኮንፌዴሬሽኑ በይፋ መቀላቀሏ ለአህጉራዊው እንቅስቃሴ ትልቅ ጉልበት ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የኮንፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር ኪይካማቱዋ (ዶ/ር) ናቸው።
ፌስቲቫሉ ውድድር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ባህላዊ እሴቶች በስፖርት አማካኝነት ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝና የአፍሪካን ማንነት፣ አንድነትና ሰላም የምናከብርበት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።
የሁለቱ ተቋማት ስምምነት በቴክኒክ ድጋፍ፣ በሚዲያ አጠቃቀም፣ በባህላዊ ጨዋታዎች ሕጎች ዝግጅትና ስልጠና ዙሪያ በቅርበት ለመስራት የሚያስችል ሲሆን፥ ኢትዮጵያ በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክርም ተገልጿል፡፡
ፌስቲቫሉ መላው አፍሪካውያን የየራሳቸውን ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ይዘው የሚቀርቡበት፤ የአህጉሪቱ ወጣቶች የሚገናኙበት እና የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት ደማቅ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በተሾመ ኃይሉ

