አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመከላከያ ሰራዊት የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የ107 ሺህ ዶላር ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢስቲትዩት እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) መካከል የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ፊርማ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ አዛዥ ኮሎኔል ጌቱ ታዬ ገንዘቡ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ዘርፍ የሚማሩ የማስተርስ ፕሮግራም ተማሪዎችን አቅም ለማሳደግ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኤንዲፒ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ስምሪት ላይ ያላትን ተከታታይና አስተማማኝ ተሳትፎ አድንቀዋል።
በሰላም ማስከበር የሚሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት በሥነ ምግባርና በጽናት የሚታወቅ መሆኑን ገልጸው÷ ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ድጋፉ የአፍሪካን የሰላም ማስከበር አመራር ለማጠናከር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን ወታደራዊ አታሼ ኦራ ሱቶም የጃፓን መንግሥት ከዚህ ቀደም ከተባበሩት መንግሥታትና ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር ለኢንስቲትዩቱ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
ጃፓን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኢንስቲትዩቱን ጥራትና ውጤታማነት ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

