Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አበባ የሆነችው አዲስ አበባ…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በፈረንጆቹ 2025 መጋቢት ወር ከጆሃንስበርግ ከተማ ምክር ቤት ተወካዮች ጋር ውይይት ሲያካሂዱ ለንግግራቸው መነሻ ያደረጓት አዲስ አበባን ነበር።

ፕሬዚዳንቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተመለከቱት የለውጥ ጉዞ እጅግ የሚደንቅ መሆኑን በመጥቀስ የከተማዋን ለውጥ በአድናቆት አንስተዋል።

በወቅቱ በመድረኩ ባደረጉት ንግግርም ‘በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማን ጎብኝቼ ነበር፤ ከተማዋ እጅግ ምቹ፣ ውብ እና ጽዱ እንደሆነች አይቻለሁ። ኢንቨስትመንት እና ንግድን ተሟሙቆባታል ብለዋል።

“አዲስ አበባ የምታምር ከተማ ሆናለች። ዛሬ በአዲስ አበባ ስትንቀሳቀሱ የደመቁ ሰፊ እና ጽዱ ጎዳናዎች ታያላችሁ፤ የንግድ እንቅስቃሴውም እያደገ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ የፕሬዚዳንት ራማፎሳ የአድናቆት ምስክርነት ሌሎች አዲስ አበባን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጎበኟት ሁሉ የሚሰጡት ምስክርነት ሆኗል።

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመዲናዋ የተወያዩት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አሁና ኤዚያኮንዋ የከተማዋን ውበትና ለውጥ አሞካሽተዋል።

አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በተጀመረው የመልሶ ማልማት ሥራ መደነቃቸውን በመግለጽ፤ በከተማዋ ልማት የነዋሪዎች ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ አካታች የልማት ስትራቴጂ ተተግብሯል ብለዋል።

የአዲስ አበባ የልማት ጉዞ በአፍሪካ ከተሞች እንደ ልምድ ሊስፋፋ እና አዲስ አበባም ሚናዋን ልትወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል።

መዲናዋ ባስተናገደቻቸው ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ መድረክ ለመሳተፍ እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በአዲስ አበባ የተገኙ መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የድርጅት መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጎብኚዎች ሁሉ የከተማዋን ሁለንተናዊ ለውጥ ከማድነቅ ወደኋላ አላሉም።

የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚዬም እና ሌሎች ሥራዎች የመዲናዋ የለውጥ ትሩፋት ናቸው።

በዐቢይ ጌታሁን

Exit mobile version