አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከኤምሬቶች የፍትህ ሚኒስትር አብዱላህ ቢን ሱልጣን ቢን አዋድ አል ኑአይሚ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሁለትዮሽ የሕግና የፍትህ ትብብር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን÷ አምባሳደር ጀማል በዚህ ወቅት ኢትዮጵያና ኤምሬቶች በቃልና በተግባር የተሳሰሩ ወንድማማች ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከኤምሬቶች ጎን በጽናት እንደምትቆም አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በፍትህ ሥርዓቷ ላይ እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራ ዙሪያም ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በተለይም የፍትህ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ፣ የዳኝነት ነፃነትን ለማረጋገጥና የሕግ ማዕቀፎችን ከዘመኑ ጋር ለማጣጣም እየተደረገ ያለውን ጥረት ጠቅሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የፍትህና የሕግ ማዕቀፎች በማቀናጀት የዜጎችን መብትና የባለሀብቶችን ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል።
አብዱላህ ቢን ሱልጣን በበኩላቸው÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ወደ ኤምሬቶች ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ ጉብኝታቸው በቀጣናው እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅት የተደረገ በመሆኑ በሁለቱ ሀገራት ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጠውና የማይረሳ ነው ብለዋል።
ተቋማቸው ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በሀገራቱ መካከል የሚደረገውን የሕግና የፍትህ ትብብር የሚያጠናክር፣ የልምድ ልውውጥን የሚያበረታታ እና ለሁለቱም ወገኖች የሕግ ባለሙያዎች ዘላቂ ግንኙነት የሚፈጥር ስትራቴጂካዊ የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር መስማማታቸውን ኤምባሲው ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።

