አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለፋሲካ በዓል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለሩሲያ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚከበረውን የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ሀገራቸው ለተኩስ አቁም ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ የተከሰተውን ጫና ለመቀነስ በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ለፋሲካ በዓል የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ ነን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ስለ ሰው ሕይወት የሚያስብ ማንኛውም አካል ግጭቱ በዘላቂነት እንዲቆም ማሰብ አለበት ብለዋል፡፡
ሉዓላዊነታችንን እና ክብራችንን የማይነካ ከሆነ ማንኛውንም አይነት የስምምነት ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነን ነው ያሉት፡፡
ኬቭ በሩሲያ የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች እንድታቆም አጋር ሀገራት ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ጠቁመው፥ ሩሲያ መሰል ጥቃቶችን የማትፈጽም ከሆነ ሀገራቸውም የቀረበውን ጥሪ እንደምትቀበል አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት የዩክሬን ወታደራዊ ኃይሎች የሩሲያ የነዳጅ ክምችት በሚገኝበት የባልቲክ ወደብ ላይ የድሮን ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ

