አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለተኪ ምርት በተሰጠው ትኩረት ዘርፈ ብዙ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በተኪ ምርት 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን የተቻለ ሲሆን÷ ዘንድሮ ደግሞ 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ለማዳን ታቅዶ እየተሰራ ነው። በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ ተመላክቷል።
ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ፣ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻልና ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ተኪ ምርት ጉልህ ሚና እንዳለውም ታምኖበታል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተኪ ምርት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመቅረፍ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡
በዚህም ቀጣይነት ያለውን ዕድገት እያሳየ የመጣው ተኪ ምርት የማምረት ሥራ ውጤቱን ይበልጥ ለማጠናከር ኢንቨስትመንት እና አምራች ኢንዱስትሪን የሀገሪቱ የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ተኪ ምርት የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲሁም ፈጠራን እና ለአምራች ኢንዱስትሪው እሴት መጨመርን የሚያበረታታ ሥነ ምህዳር ለማዳበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
እንደ “ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ባሉ ኢኒሼቲቮችና ትግበራዎች ቀጣይነት ያለው ዘርፈ ብዙ ዓላማዎችን ለማሳካት ሰፊ ርብርብ ተደርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን ለማሳደግ በሚሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
አምራች ኢዱስትሪዎች ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ያሉባቸውን ማነቆዎች መለየትና የፖሊሲ መፍትሄ አቅጣጫ የማስቀመጥ ስራ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተሰርቷል፡፡
ከኃይል አቅርቦት፣ ከግብዓት እጥረት እና ከፋይናንስ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመፍታትም በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተለይ እንደ ሀገር ያለውን አቅም መለየትና ገቢ ምርቶችን ለመተካት እየተሰራ ሲሆን÷ በዚህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ምርቶችን ለመሸጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ ሰፊ የስራ እድል መፍጠርና ዜጎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል፡፡
ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ ተኪ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
መንግስት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን በበቂ ሁኔታ ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
የሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋና ማሳያ የምርት እድገት በመሆኑ መንግስት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ ተኪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

