Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ በደረሰው የመኪና አደጋ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተባበሩት አደባባይ አካባቢ በደረሰ የመኪና አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በ3 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ቶማስ እሸቴ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የትራፊክ አደጋ የተከሰተው በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 1 ሰዓት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው የተባበሩት አደባባይ ነው።

በአደጋውም የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በሦስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

አደጋው የአልያንስ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከአቤም ወደ የተባበሩት አቅጣጫ ቁልቁለቱን በመጓዝ ላይ ሳለ ከአያት ወደ ሲኤምሲ አቅጣጫ እየተጓዙ የነበሩ ቪትዝ እና ፒካፕ ተሽከርካሪዎችን በመግጨቱ እንደተከሰተ ገልጸዋል።

በአደጋውም የፒካፕ መኪናው አሽከርካሪ ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በውስጡ ተሳፍረው የነበሩ ሁለት የ7ኛ እና የ5ኛ ክፍል ሴት ተማሪዎች እንዲሁም የቪትስ መኪናው አሽከርካሪ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version