Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዝቡ ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የነዳጅ ችግር ለመቅረፍ አውስትራሊያውያን ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሜሪካ-እስራኤል እና እራን ጦርነት በዓለም ዙሪያ በነዳጅ እና በናፍጣ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳስከተለ ገልጸው÷ አውስትራሊያ የጦርነቱ አካል ባትሆንም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች እየተጎዱ መሆኑንና መንግሥትም ተፅዕኖውን ለመቀነስ የተለያዩ ርምጃዎች እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሰዎች እርስ በርስ በመተሳሰብ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ነዳጅ መግዛት እንዳለባቸውና በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ በማሳሰብ እንደ አውቶቡስና ባቡር ያሉ የሕዝብ ማመላለሻ አማራጮችን እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።

ነዳጅን መቆጠብ በየቀኑ ነዳጅ የሚያስፈልጋቸውን ዘርፎች እንደሚረዳ አንስተው÷ በጦርነቱ ምክንያት የሚመጡት ወራት አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ መናገራቸውን ሰቨን ኒውስ ዘግቧል።

በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኘው ጦርነቱ በርካታ ሀገራት የነዳጅ አጠቃቀማቸውን እንዲያሻሽሉ እያደረገ ሲሆን÷ ኢትዮጵያም ነዳጅ በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻለ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

በዚህም የነዳጅ አቅርቦት እጥረቱ በሀገርና በዜጎች ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድር በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ አሳልፏል።

በውሳኔውም ነዳጅ እና መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች፣ ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ ፕሮጀክቶች፣ ትራክተሮች፣ የብዙኃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር እንዲተገበር መመሪያ አውርዷል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version