Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ 5ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ አምስተኛውን የ”አዲስ መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ በሀገራዊ ለውጡ ስምንተኛ ዓመት ዋዜማ ላይ በአዲስ አበባ አምስተኛውን የ”አዲስ መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ማዕከል በይፋ ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።

አዲስ አበባ አሁን የደረሰችበት ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነት የተመዘገቡ የመጋቢት 24 ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ መዲናነት ተሻግራ የአፍሪካ ኩራት የሆነችውን አዲስ አበባን በተግባርም እንደ ስሟ ውብ ለማድረግ የለውጡ መንግሥት ገቢር ያደረጋቸው የልማት ሥራዎች ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ ስኬትን አስመዝግበዋልም ነው ያሉት።

ከለውጡ መንግሥት ስኬቶች መካከል አንዱ የ”አዲስ መሶብ” ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ የመንግሥት ሥርዓታት በተለዋወጡ ቁጥር ቃል እየተገባ ለመለወጥ ጥረት ቢደረግም ሳይለወጥ ቆይቶ ተገልጋዩን ሲያማርር የኖረውን ስር የሰደደና በተንዛዛ ቢሮክራሲ የተተበተበውን አሰራር ከመሠረቱ የሚቀይር ነው ብለዋል።

ጊዜ፣ ወጪና ጉልበት የሚባክንበትን እንዲሁም ጥራትና ቅልጥፍና የራቀውን አገልግሎት አሰጣጥ በተግባር በመለወጥ አዲስ ምዕራፍ መክፈት መቻሉንም አብራርተዋል።

“ማገልገል ክብር ነው” በሚል መርህ በንጹህ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ በንጹህ አዕምሮ እና በንጹህ እጅ ማገልገልን ይዞ መጥቷል ሲሉም አስረድተዋል።

ዛሬ የተጀመረው የአዲስ መሶብ ማዕከል፣ መርካቶን ጨምሮ ሰፊ የንግዱ ማህበረሰብ የሚንቀሳቀስበት አካባቢ በመሆኑ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ እፎይታን የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል።

እያሰፋን ያለነው የዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከከተማችን ነዋሪዎች ባሻገር ለዲፕሎማቶች፣ ለቱሪስቶችና ለኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ጭምር ነው ሲሉም አመላክተዋል።

የአንድ መስኮት ዲጂታል አገልግሎቱ በታለመለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ለደገፉት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

Exit mobile version