አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በለውጡ ለተገኘው ድልና ስኬት እውቅና የሚሰጥ ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።
በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የሰበታ፣ ፉሪ፣ ኮዬፈጬ፣ ገላንጉዳ፣ የካጣፎ፣ ሱሉልታ እና ቡራዩ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ነው የድጋፍ ሰልፉ እየተካሄደ የሚገኘው።
ሰልፈኞቹ በመልዕክቶቻቸው ከመጋቢት እስከ መጋቢት የተመዘገቡ የስኬት ጉዞዎችን በመግለጽ፤ በመጋቢት 24 ተምሳሌታዊ ጉዞ እና መሰረታዊ ርምጃ የተመዘገቡ ስኬቶችን እያደነቁ ነው።
በለውጡ መንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን በመደገፍ፣ በቀጣይም የተሻለ ስራ እንዲሰራ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የሚያረጋግጡ መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛል።
በዚህም በመጋቢት 24 ፍሬ ወደ ተምሳሌታዊ ጉዞ፣ ጠንካራ መሰረት የተምሳሌትነት ጉዞ ስንቅ፣ መሰረት ባለው ርምጃ ወደ ተምሳሌትነት፣ መጋቢት 24 የተምሳሌታዊነታችን መሰረትና መፍለቂያ ነው፣ የመጋቢት 24 ፍሬዎች የተምሳሌትነት ጉዞ የትውልድ ብልፅግና ነው የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በተጨማሪም መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ለውጥ መነሻና ብልፅግና መሠረት ነው፣ መጋቢት 24 በመስዋዕትነት መጣ በመስዋዕትነት እንጠብቀዋለን የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።
በሄኖክ ለሚ

