Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከቻይና ህዝባዊ ባንክ ገዥ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከቻይና ህዝባዊ ባንክ ገዥ ፓን ጎንግሼንግ ጋር የፋይናንስ አጋርነትን ለማጠናከር ያለመ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይታቸውም የሁለቱን ተቋማት የንግድና ኢንቨስመንት ትብብር እና የፋይናንስ አጋርነት ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሰረት እያደረገች ያለውን የዕዳ ሽግሽግ ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተደረጉ ስኬታማ ተግባራትንና የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶችን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች የገቢ ምንጮችን በመጠቀም እንዲሁም ቁልፍ የወጪ ንግዶችን በቻይና ዩዋን በማከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያለውን የቻይና ዩዋን ክምችት የማሳደግ አቅም መኖሩን አንስተዋል፡፡

ይህ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቻይና ኢንተርፕራይዞችን የስራ አካባቢ የሚደግፍና አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመሳብ የሚያግዝ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ፓን ጎንግሼንግ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ድንበር ተሻጋሪ የባንኮች የክፍያ ሥርዓትን (ሲአይፒኤስ) የሚቀላቀሉበትን እድል በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም የንግድ ስርዓትን ማቀላጠፍ የሚያስችለውን የቻይና ዩኒየን ፔይ የክፍያ ሰርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ስለሚቻልበት ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የረዥም ጊዜ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ሰምምነት ላይ መድረሳቸውን ብሔራዊ ባንክ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version