አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የ2018 የበጀት ዓመት የስምንት ወራት እቅድ አፈጻጸም መነሻ በማድረግ የቀረበለትን የበጀት ክለሳ አፅድቋል።
ካቢኔው በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ አማካኝነት የቀረበለትን ከ523 ሚሊየን 603 ሺህ 565 ብር የበጀት ክለሳ ነው ተወያይቶ ያፀደቀው።
የበጀት ክለሳው የፊዚካልና ፋይናንሻል አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመለየት የላቀ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ላላቸውና የበጀት እጥረት ላጋጠማቸው ጉዳዮች የሚውል መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ለገጠር ሞዴል የአርሶ አደሮች ቤት ግንባታ ፕሮጀክት፣ ለገጠር ትስስር ተደራሽንነት፣ ለምግብ ዋስትናና ለመደበኛ ስራዎች ማስፈጸሚያዎችን በመለየት የበጀት እጥረት ላጋጠማቸው ጉዳዮች የሚውል ነው ተብሏል።
ከበጀት ክለሳው በተጨማሪ ካቢኔው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጡን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

