Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዚያ 14 አራዝሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ማራዘሙን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በጊዜ ሠሌዳው መሠረት ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያከናውን ማሳወቁ ይታወቃል፡፡

ቦርዱ የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ ሥርዓትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማከናወን ባወጣው ዕቅድ መሠረት በአሁኑ ወቅት የዕጩዎችን ምዝገባ አጠናቅቋል፡፡

በጊዜ ሠሌዳው መሠረት ቦርዱ የመራጮች ምዝገባን እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን÷ በዚህ ሂደት ውስጥ፡-

✓ በተያዘው ዕቅድ መሠረት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የመራጮችን ምዝገባን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የኔትዎርክ አቅርቦት እና በምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በፍተሻ ሥርዓት እየለዩ ሲስተሙን አስተማማኝና ቀልጣፋ ለማድረግ ሂደቱ የጠየቀውን ጊዜ ማካካስ በማስፈለጉ፣

✓ የኔትዎርክ አቅርቦታቸው አስተማማኝ ነው ተብለው የቀረቡ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የኔትዎርክ አቅርቦት አለመኖሩ በተጨባጭ በመታየቱ ወደ ማንዋል በመቀየር ሂደት ለባከነ ጊዜ ማካካሻ በማስፈለጉ እና

✓ በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በትራንስፖርት አቅርቦት ምክንየት የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ በወቅቱ ባለመድረሱ የተፈጠረውን የመራጮች ምዝገባ መዘግይት ማካካስ አስፈላጊ በመሆኑ ቦርዱ የመራጮችን ምዝገባ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም አራዝሟል።

በምርጫዬ የሞባይል መተግበሪያ ራስዎን ለመራጭነት ይመዝግቡ!

● ከአፕ-ስቶር:- https://url-shortener.me/IHPC
● ከፕለይ-ስቶር https://url-shortener.me/IHPF ላይ በማውረድ ወይም
●በድረ-ገጽ አማራጭ (በቀጥታ) https://url-shortener.me/IHPH ይመዝገቡ።

Exit mobile version