አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት የታየበት ኮንፈረንስ ቱሪዝም የሀገር ገጽታን ለማስተዋወቅ ከፍ ያለ ፋይዳ አለው አሉ።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ምሰሶ የሆነውን ቱሪዝም ለማሳደግ በተሰራው ስራ የላቀ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማሳደግና ከማጎልበት ባሻገር ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም 16ኛውን አህጉራዊ ኮንፈረንስ ለማስተናገድ ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት አድርጋለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የአዲስ አበባን የኮንፈረንስ ማዕከልነት ያጎሉ በርካታ ኮንፈረንሶች መስተናገዳቸውን አስታውሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 153 አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ ዘንድሮም በተመሳሳይ በርካታ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።
ከቱሪዝም ሁሉ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለውን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዓቅም ለመጠቀም በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸው፤ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ለቱሪዝሙ የሚመጡ እንግዶች በተለይም የሚዲያ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ገጽታ አጉልተው የሚያስተዋውቁበት ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል።
መጋቢት 30 እና ሚያዚያ 1 ቀን 2018 ዓ በአዲስ አበባ ከተማ በሚስተናገደው የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም 16ኛውን አህጉራዊ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ በአደጋ ስጋት አስተዳደር በተለይም በሰብዓዊ ድጋፍ ራስን ለመቻል ባደረገችው የተመዘገበው ስኬት ለመድረኩ በተሞክሮነት እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የመድረኩ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ።
በአቢይ ጌታሁን

